የህልሜ ቀን - Dream Day
የህልሜ ቀን - Dream Day
የሆነ ቀን ከረፋዱ የጀመረው ዝናብ ጉልበቱ ቢቀንስም አሁንም ሰማዩን አላስረክብም ብሎ በደከመ አቅሙም ቢሆን ተያይዞታል
ሲኒማ ኢትዮጵያ ስር ካሉት ካፌዎች በአንዱ ውስጥ ጥጌን ይዣለሁ [እንደሁሌው] ..... ጋዜጣም ይዣለው [እንደሁሌው]..... ቡናም አዝዣለው[እንደሁሌው]... ...ፒያሳ ነኝ የመሃሊቱ እምብርት ስር......
እየጠበኩዋት ነው... መጠበቄን እወደዋለሁ...እንደሁሌው እየጠበኩዋት ነው ለኔ መጠበቄ የፍቅሬ ልኬት ነው... ፍቅሬን ምሰፍርበት...
ገጣሚው...
"የሚወዱትን ሰው ቀጥረው ካረፈደ
የሚያፈቅሩት ሰው ቀጥረው ካረፈደ
ነገር ተበላሸ ህመም ተወለደ "
.....................ባለው አልስማማም ለኔ በመጠበቅ ውስጥ ማሰብ:ተስፋ: ትዕግስት: ሕይወት አለ .......ደግሞስ የጠበቁት ነገር አይደል ይበልጥ የሚወደድ... ልጅንስ አቅፈን ምንስመው የዘጠኝ ወር ጥበቃ አስበን አይደል :
እኛ ሀበሾች ከሻይ ይልቅ ቡናን ምንወድ በመጠበቅ ውስጥ ያለንን ደስታ አስበንም አይደል
እጠብቃታለሁ...እየጠበኩዋትም ነው... እሷን ይዞ ሚመጣውን ባስ ግን......
አሻግሬ የሷን ባስ ቁጥር እየፈለኩ ነው... ዛሬ ግን ያለወትሮዋ ቆየች... እኔም ትግስቴ ሰነፈች መሰለኝ... ዛሬ የመገናኘታችን ምክንያት ትያትር ነው... ላለፉት ስድስት ወራት ስጠብቀው የነበረው ትያትር ዛሬ ለመድረክ ይበቃል እና እሱን ለማየት ልቤ ተሰቅሏል..... እንደው ልቤ በስንቱ ነገር ይሰቀል... ትግስቴም የሰነፈችው ለ ትያትሩ በመጓጓቴ ይሆናል
መጣች.... ባሷ... ከካፌው ፍንጥር ብዬ ተነሳው.. ሮጥኩም መሰለኝ " ሰውዬው" የካፌው አሳላፊ ነው የጠራኝ .....ወይኔ ቅሌቴ ሂሳቤን ሳልከፍል....
ያቻት እሷ... ልቤን ውጋት ያዘኝ... ዛሬ ደሞ እንዴት ነው ያማረችው.... አበባ ትመስል... እግር ቆጠራዬ ጠፋብኝ... ዝነጣዬ ተምታታ .. የሸሚዜ ቁልፍ ተዛነፈ... ተርበተበትኩኝ... ወደ እኔ እየመጣች ነው.... አልቻልኩም.... ልቤ የመሄድ አቅም አጣች.... ቆሜ ጠበኩዋት... ንፋሱ ደግሞ ምን ሊያረጋት ነው.... ፀጉሯን ይበትነዋል ቀሚሷንም ሊገፋትም ይዳዳዋል.... አረ ተው ንፋስ... ለኔም የልኬን ላከልኝ በአይን ርሃብ ከምሰቃይ... መጥታ ከውስጤ ገባች... እኔስ ሳምኳት መሰለኝ.... ደስ ስትል.... ደስ የሚል ነገር ግን ደስ ሲል.... እጅ ለእጅ ተቋልፈን.... ወደ ሀገር ፍቅር ትያትር አቀናን....
ምነው እቺ ሰዓት ዘላለም ብትሆን
ዘላለምም ይቺን ሰዓት ቢሆን
የሁለት ሰው ትኬት ቆረጥኩ... ያስለመድነውን የትያትር ቁርስ(ልክ እንደ ቡና ቁርስ)... Sunchips.... ለሷ ፋንታ ለስላሳ ለኔ ኮካ ያዝን እና ወደ ትያትሩ አዳራሽ ገባን... የራሳችን ቦታ አለችን.... ወደዛ ሄድን እዛችው ተመቻቸን.... አላረፈድንም... ልክ.... በሰዓቱ... መብራቱ ጠፋ... ሁሉም ነገር ፀጥ አለ... የኔው መከረኛ ልብ ድው ድው ሲል ሰማዋለው ኧረረ አንዳንዴ እንኳን እረፍት ይሰማህ... ለምድነው ግን የምንወደው ሰው እንኳን አጠገባችን ሆኖ ልባችን ሚታፈንብን...... እውነት መውደድ ግን ረፍት የለሽ ነው
ትያትሩ ላይ ሁሉም ልቡን ጥሏል.... ዞር ብዬ አየሁአት የመድረኩ መብራት በ ወጋገን ከፊቷ ገፅ ላይ አርፎ ደሞ የሰጣት መልክ... የጋለ ወርቅ ይመስል... ሞቀችኝ... ውስጤን ሞቀኝ... እጄን አላበኝ... እጄን ሰደድ አድርጌ እጇን አጥብቄ ያዝኳት... ዞር ብላ የብርጓድ በመሰሉ አይኖችዋ አየችኝ አየኋአት....... ቀስ ብላ ተጠጋችኝ አይኔን በስሱ ሳመችኝ... "አርፈህ አታይም " ስትል በጆሮዬ ተስለመለመች.... ጭራሽ ደነዘዝኩ.... ከንፈሯ... ለስላሳ እና እርጥብ ነው... ይቀዘቅዛል
ወይኔ እኔ
ከትያትር አዳራሽ እየወጣን ነው... ከዛም ፊታችንን አዙረን ቁልቁል በቸርችል ጎዳና እያዘገምን ነው ሁሌም በዚ ጎዳና ስንጓዝ ወደ ሃሳቤ ሚመጣብኝ ነገር ሁሉም ነገር ከፍ ብለው ሲያዩት ማማሩ.... በጨለማ በጨረቃ ብርሃን ታግዞ ሁሉም የቆመው ነገር ሁሉ ነፍስ ዘርቶ ስለ ውበት ሰልፍ ይይዛል...
ከትያትር ስወጣ ሁሌም አንደበቴ ዝም ይላል... ውስጤ ተረጋግቶ መንቀሳቀስ ያቆማል... እንደው ሁሉ ነገሬ ፀጥ ይላል....እሷ ደግሞ ከሁልጊዜ ቀፎዋ ውስጥ ትወጣና መክነፍ ትጀምራለች ከፍ.... ከፍ.... ትላለች በደስታ ታበራለች
እንደዛ ስትሆን ደግሞ ይበልጥ ማማሯ...
ስለ ትያትሩ የተሰማትን ታወጋኛለች.... እኔም ዝም ብዬ አዳምጣለሁ... ለኔ ክፍያዬ ይሄ ነው.... የዛ ሁሉ ጥበቃ ደሞዜ
ውብ ትያትር አይቶ ደሞ ሌላ ትያትር በውብ መልክ በውብ እመቤት ሲቀርብ.... መታደል ነው.... ታድያታለው
በኔና በሷ ሂወት ውስጥ ንድፍ - pattern ቦታ አለው ሁሉም ነገራችን በንድፍ ውስጥ የተጠለፈ ነው... ለዛም ነው ሚጥመኝ... አሁን ብሔራዊ ትያትር ስንደርስ.... Photo አንሳኝ ትለኛለች.... አነሳታለው...
... ፎቶዋን ወደደችው...አመሰግናለሁ ብላ ጉንጬን ሳመችኝ
እዛው አከባቢ ካለው "ጫካ ቡና " ከላይኛው ሰቀላ ከጥገኛው ስፍራ ርስታችንን ይዘናል... እንደሁሌው... እኔ ቡና አዘዝኩ እሷ ስፕራይት በውሃ... እንደሁሌው... ምናለ ሁሉ ነገር እንደሁሌው ቢሆን ግን ከእሷ ጋር ...
በመስኮቱ አሻግረን ወጪ ተራማጁን እያማተርን ነው.... በዚህ መስኮት ውስጥ የማየው ውበት ለኔ ያልተፈታ ቅኔ ነው.... ልዩ ውበት.... ባየው ባየው የማይሰለቸኝ... ተቀምጨ ብውል ማይቆረቁረኝ.... ቁጭ ብዬ ባድር ማይደክመኝ.... ለዚህ ውበት ለዚህ ሰላም ምንም እከፍላለሁ.... ለእኔ ይሄ የህልሜ ቀን - Dream Day ነው
በዚህ ላይ እሷ ኖራበት ማበድ እኮ ነው...
ውበትን አቅፎ አማትሮ ማየት
ውበትን አፍቅሮ አይቶ መደሰት
ይሄን ይሄን ጊዜ አንቺን ይዞ መቃተት
ብቻ መታደል ነው: ብቻ መታመም ነው.... ቆንጆ ሴትን በቆንጆ ምሽት ይዞ ማምሸት.. ያማል-ደስ ደስ ሚል ህመም
ባይመሽ ባይነጋ
ካንቺ ጋ
ልክ እዚህ ጋ
Comments
Post a Comment