በሳምንት አንዲት ሴት ለማናውቀው አምላክ?!
በሳምንት አንዲት ሴት ለማናውቀው አምላክ?! (አሌክስ አብርሃም) እንደቀልድ ዓይናችን እያያ ከሦስትና አራት ሺ ዓመታት በፊት ወደነበረው የማያ ዘመን "ክፉ አምልኮ" ተመልሰናል። በዚያ ዘመን አንዲት ሴት ትመረጥና ራሷን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ እጇ ተጠፍሮ መሰዊያው ላይ ትቀመጣለች። ትፈራለች፣ አድኑኝ ትላለች፣ ትንቀጠቀጣለች፣ ወላጆቿን፣ ዘመዶቿን፣ ያደገችበትን ህዝቧን፣ እነዛን አገርና ህዝብ ይጠብቃሉ ብላ የዘፈነችላቸውን ፈርጣማ ወታደሮች ትማፀናለች። ግን ማንም አያድናትም። "ዝም በይ አምላክ ይቆጣል እየሳቅሽ ሙች" ፣ ትባላለች። "የአምልኮ ስርዓቱን አትረብሽ" ትባላለች። በለመደ አጋፋሪ ደም ስሯን በሹል ብረት ትወጋና ደሟ ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ መሰውያው ላይ ይፈሳል። በስቃይ ስትወራጭ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ያለቅሳል፣ ሰበዓዊነት የተሰማው ሲቃ ይይዘዋል፣ በተቃራኒው አንዳንዱ ለተሰዋለት አምላክ ጥብቅና ይቆምና ሁሉም ዝም እንዲል ያዛል። ሌሎች እልልታና ውዳሴ ያቀርባሉ። ሲቆይ እንባውም እልልታውም አምልኮውም ያልቅና ድል ያለ ድግስ ተበልቶ ህዝቡ ይበተናል። ቀጣይ መስዋዕት ማናት? የእልል ባዮ፣ ወይም የአልቃሹ ወይም የሚሰዋለት አምላክ አገልጋይ ሴት ልጅ ልትሆን ትችላለች። ግን የመሰዊያው ቀን እስኪቃረብ ሁሉም ረስቶት ሲስቅ፣ ሲጫወት፣ ሲሰራ፣ ሲዘፍን ይከርማል። መስዋዕቱ የሚቀርብበት ምክንያት ብዙ ነው፣ ዝናብ ከጠፋ አንዲት ሴት ትሰዋለች፣ ጦርነት ከመጣ አምላካቸው ድል እንዲሰጣቸው ሌላ ሴት፣ ንጉሱ ወይም የንጉሱ ወንድ ልጅ ከታመመ እንዲድን ሌላ ሴት ትገደላለች... ይሄው በዚህ ዓመት እኛም እንደአገር በአማካኝ በሳምንት አንድ ሴት "ለማናውቀው አምላክ" "በማይታወቁ አካላት" አጋፋሪነ...